ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፍራንክፈርት ኮሜርዝ ባንክ አሬና ስቴድየም ለኢትዮጵያውያን ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ አንኳር ነጥቦች፡-

ሀገራችን ከአውሮፓውያን ጋር ከጥንት ጀምሮ የቆየ ታሪካዊ ትስስር አላት፡፡ ይህ ለዛሬው ግንኙነታችን መሰረት ጥሏል፡፡
• ጀርመናውያን በዓለም ጦርነት ወድማ የነበረችውን ሀገራቸውን መልሰው ለመገንባት የወሰደባቸው ከ40 ዓመታት ያልበለጠ ጊዜ ነው፡፡
• አውሮፓውያን እርስ በርስ ከመሸናነፍ ይልቅ ድህነትን ማሸነፍን በመምረጣቸው ዛሬ እዚህ ደርሰዋል፡፡ ይህ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል፡፡
• ዛሬ ያላየነውን የምናይበት ያልሞከርነውን የምንሞክርበት ጥርሳችንን ነክሰን የምንሰራበት ወቅት ነው፡፡
• ኢትዮጵያ ማንም በየጊዜው እየተነሳ እንደ ቂጣ ጠፍጥፎ የሚሰራት የግል ርስት ሳትሆን ዘመናትን ያስቆጠረች ታላቅ ህዝብ የመሰረታት ታላቅ ሀገር ናት፡፡
• “እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው” ዓይነት ሊደርጓት ለሚሹ – ኢትዮጵያ አንቀላፍታ ደክማ ይሆናል እንጂ አልሞተችም፤ ቀጥናለች እንጂ አልተበጠሰችም፡፡
• ኢትዮጵያዊነትን ከስሜት በዘለለ በስራ የምንገልፅበት ወቅት ላይ ነን፡፡
• ከትናንት አያሌ መልካም ነገሮች እንደወረስን ሁሉ ብዙ መለወጥ ያለባቸውም አሉ፡፡
• ዛሬንና ነገን ጥሩ የምናደርገው ስለትናንት በመነታረክ አይደለም፡፡
• እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁ እንጂ እነእገሌ ሀገሬን ጉድ ሰሯት ከማለት ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡
• ጠንክረን ካልሰራን ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲሁ አይመጣም፡፡ ተደምረን ተግተን ስንሰራ ብቻ ነው ይህ እውን ሊሆን የሚችለው፡፡
• ለዚሁ ዓላማ ተቋማትን በመገንባት ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ የሚ
ወጡ ሰዎች በመመደብ ላይ እንገኛለን፡፡
• በምርጫ ቦርድ፣ መከላከያ፣ ፍትሕ፣ ትምህርት ወዘተ ተቋማት አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡
• በቅርቡ በፍትሕ ዘርፉ ላይ ወሳኝ የሆኑ የማስተካከያ እርምጃዎች እንወስዳለን፡፡
• ለነገው ትውልድ የምትሆን ኢትዮጵያን የመገንባት ፈታኝ ስራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡
• የወር ደመወዛችሁን አስይዛችሁ እንድትበደሩልን ሳይሆን በቀን ከ1 ማኪያቶ 1 ዶላር እንድትሰጡን በድጋሚ እንለምናችኋለን፡፡
• ለሀገራችሁ እውቀትን አሸጋግሩ፡፡ በምትችሉት ሁሉ ህዝባችሁን ደግፉ፡፡ ሰው በማገዝ እንጂ በማማረር የእናቱን ቤት ማስተካከል አይችልም፡፡ በብሔር ሳንከፋፈል አንድ ሆነን ዛሬ እንነሳ፡፡
አሁን በእጃችን ያሉት ሁለት ነገሮች ነፃነትና ተስፋ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለት ነገሮች ይዘን በጋራ ከሰራን የምንመኛትን ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ የሚያግደን አንዳች ኃይል የለም፡፡
• ዛሬ ላይ በርትተን በመስራት የበለፀገችውን የነገዋን ኢትዮጵያ አብረን እንገንባ፡፡
• አንድ ቀን ፍልሰቱ ወደ አውሮፓ መሆኑ ቀርቶ ወደ እምዬ ኢትዮጵያ ይሆናል፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስደቱ ለኑሮ መሆኑ ቀርቶ ለጉብኝት እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *